✅ሆሳዕና ላይ የአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ እና ሰኞ የተካሄዱ ሲሆን የመጀመሪያ የነበረው የዳሞት ከተማ አና የሮቤ ከተማ ጨዋታ በሮቤ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሮቤ ከተማ ከተከታታይ 3 ጨዋታ ሽንፈት በኋላ የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል።
✅ሁለት ግብ የተመለከትንበት የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ በእንቅስቃሴ ረገድ ፈጣን የሆነና በግብ ሙከራ የታጀበ ሲሆን በጨዋታው የመጀመሪያ 10 ደቂቃ የዳሞት ከተማ የበላይነት የታየበትና ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች እና የግቡ አግዳሚ የመለሰባቸው አጋጣሚ ይጠቀሳል። በ5ኛው ደቂቃ ሮቤ ከተማዎች ያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት በአማን ወርቁ አማካኝነት የመጀመሪያ ግባቸውን አስቆጥረዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ሮቤ ከተማዎች ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ተጭነው በመጫወት እና ዳሞት ከተማዎች በበኩላቸው የሮቤ ከተማዎችን ጫና ለመቋቋም በማፈግፈግ የተጫወቱ ሲሆን በ13ኛው ደቂቃ ሮቤ ከተማዎች በጥሩ ቅብብል ያገኙትን ኳስ በድጋሚ በፊት መስመር ተጫዋቻቸው አማን ወርቁ በጨዋታው ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለት ግብ በማስቆጠር ሮቤ ከተማ 2-0 እዲመራ ማድረግ ችሏል። በዚህ እንቅስቃሴ ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል መግባት ችለዋል።
✅በሁለተኛው አጋማሽ ተነቃቅተው የገቡት ዳሞት ከተማዎች ውጤቱን ለመቀልበስ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን ባንፃሩ ሮቤ ከተማዎች በመጀመሪያ አጋማሽ ያስመዘገቡትን ውጤት ለማስጠበቅ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ተጫውተዋል። ዳሞት ከተማዎች ከሽንፈት ያላዳነቻቸውን ግብ በ83ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምን ሳምሶን ቁልጭ በማስቆጠር ጨዋታው በሮቤ አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።
✅የስልጤ ወራቤ እና የኮልፌ ክ/ከተማን ጨዋታ በርከት ባለ ደጋፊ ሲደገፍ የነበረው ስልጤ ወራቤ በጠባብ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። የመጀመሪያው አጋማሽ በጣም ውጥረት የተሞላበት እና ኃይል የተቀላቀለበት ጨዋታ እና ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የነበረበት ሲሆን በግብ ሙከራ ረገድ ስልጤ ወራቤ የተሻለ ሲሆን በ30ኛው ደቂቃ ሳዲቅ ሴቾ በማስቆጠር ስልጢ ወራቤ 1-0 በሆነ ውጤት እየመራ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ ማድረግ ችሏል።
✅ሁለተኛው አጋማሽ ላይም ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት ጨዋታ እና ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ኮልፌ ክ/ከተማ ግብ ለማስቆጠር ፣ በስልጤ ወራቤ በኩል ደግሞ ውጤትን ለማስጠበቅ የተቻላቸውን ሲያደርጉ ተመልክተናል። በጨዋታው መጠናቀቂያ ሰዓት አከባቢ በስልጤ ወራቤ በኩል የሰዓት ማባከን ሲስተዋል ነበር። ጨዋታው በዚህ ሁኔታ ምንም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ስልጤ ወራቤን ጣፋጭ ድል አስገኝቷል። በአንፃሩ ኮልፌ ክ/ከተማ ከሦስት ተከታታይ ድል በኋላ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ቀምሷል።
✅ደሴ ከተማ እና ሶዶ ከተማን ባገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የደሴ ከተማዎች የበላይነት የታየበትና በኳስ ቁጥጥሩም ተሽለው የታዩበት አጋማሽ ነበር ። ሶዶ ከተማዎች ጨዋታውን በማፈግፈግ እና ረጅም ኳስ በመጠቀም ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ ታይተዋል። በ31ኛው ደቂቃ ላይ በሶዶው ግብ ጠባቂ ስህተት የተገኘችውን ኳስ በአከር ቻም አማካኝነት በማስቆጠር ደሴ ከተማን መሪ አድርጎ ወደ መልበሻ ክፍል መግባት ችለዋል።
✅በሁለተኛው አጋማሽም ምንም ግብ ያላየንበት አጋማሽ ሲሆን በጨዋታውም ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ቢታይም ሶዶ ከተማዎች ከሽንፈት ሊያድናቸውን የሚችለውን ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም ማስቆጠር ተስኗቸው ሽንፈት ማስተናገድ ችለዋል። ደሴ ከተማዎችም ከእረፍት በፊት ባስቆጠሩት ብቸኛ ግብ ጣፋጭ ድል አስመዝግበው ምድባቸውን መምራት ጀምረዋል ።
✅ ሀምበርቾ ዱራሜ እና ኦሜድላን ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሀምበርቾ ዱራሜ በሙሉ የበላይነት የተጫወቱ ሲሆን በአንፃሩ ኦሜድላዎች የተጋጣሚን ጨዋታ ለማበላሸት እና ረጃጅም ኳሶችን ለመጠቀም በማሰብ ተጫውተዋል። ሆኖም በ29ኛው ደቂቃ ቃልአብ በጋሻው የመታውን ኳስ በመጭረፍ ዳግም በቀለ ሀምበርቾ ዱራሜን መሪ ማድረግ ችሏል።
✅ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ በ49ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ዳግም በቀለ በግንባር በማስቆጠር አንበሪቾ ዱራሜን 2-0 እንዲመራ ማድረግ ችሏል። ጨዋታው በዚሁ እየቀጠለ ባለበት ሁኔታ በ73ኛው ደቂቃ ታምራት አዲሱ ግሩም የሚባል ግብ በመቀስ ምት በማስቆጠር ለኦሜድላ የመጀመሪያውን ግብ የሆነና ውጤቱንም ወደ 2-1 ማጥበብ የቻለበት ነበር። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በአንበሪቾ ዱራሜ አሸናፊነት ተጠናቋል።
✅ጨዋታው ሰኞ እለት ሲቀጥል ነገሌ አርሲዎች አሰልጣኛቸውን ከቅጣት መልስ ያገኙበት የመጀመሪያ ጨዋታ እና ጅማ አባጅ ፋሮች ደግሞ አሰልጣኛቸውን ካሰናበቱ በኋላ ያደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ነበር። ጥሩ እንቅስቃሴ የታየበት ጨዋታ የነበረ ሲሆን በአርሲ ነገሌዎች የጨዋታ ብልጫ እና በጅማ አባ ጅፋር መልሶ ማጥቃት የታየበት እና በሁለቱም በኩል ጥሩ የሆነ የግብ ሙከራ የታጀበ የመጀመሪያ አጋማሽ ተመልክተናል። በ20ኛው ደቂቃ ከመዕዘን የተሻገረውን ኳስ ሱራፌል ፍቃዱ በማስቆጠር ጅማ አባ ጅፋርን መሪ ማድረግ ችሏል።
✅በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ነገሌ አርሲ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም በጅማ አባ ጅፋሩ ግብ ጠባቂ ዮሐንስ በዛብህ አማካኝነት ማስቆጠር አልቻሉም። በ47ኛው ደቂቃ የጅማ አባጅፋሩ አጥቂ ዳዊት ፍቃዱ ግብ በማስቆጠር መሪነታቸውን ማጠናከር ችሏል። በነጌሌ በኩል ሰለሞን ገመቹ ከፊት መስመር ጥሩ እንቅስቃሴ ካደረጉት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። በጅማ አባ ጅፋር በኩል ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርግ የታየው አሚር አብዲ በ61ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ግብ በማስቆጠር የጅማ አባ ጅፋሮችን አሸናፊነት ማረጋገጥ ችሏል። ጅማ አባጅፋር በምክትል አሰልጣኛቸው በመመራት ርቋቸው የቆየውን ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።
✅ የዕለቱ የመጨረሻ የነበረው የገላን ከተማ እና የቡራዩ ከተማ ጨዋታ ሲሆን በጨዋታውም ቡራዩ ከተማ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት በማሸነፍ ተከታታይ ድል ማስመዝገብ ችሏል። በመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ ትንቅንቅ እና አልሸነፍ ባይነት የታየበት ሲሆን ጨዋታው በጀመረ በ20 ደቂቃ የቡራዩ ከተማው የፊት መስመር ተጫዋች እንዳለማው ደሳለኝ ግሩም በሆነ አጨራረስ ቡራዩ ከተማን አሸናፊ ያደረገች ግብ ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ጨዋታው በእንደዚህ ዓይነት መልኩ የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል መግባት ችለዋል።
✅በሁለተኛው አጋማሽም በተመሳሳይ ውጥረት የበዛበት ጨዋታ ሲስተዋል ገላን ከተማ ከሽንፈት ለመዳን ጫና በማሳደር ግብ ለማግባት ሲሞክሩ ተስተውሏል። በአንፃሩ ቡራዩ ከተማ በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኘውን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ ወደ ኋላ አፈግፍጎ ሲጫወት ተስተውሏል። ሆኖም የገላን ከተማዎች ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ ሽንፈት ማስተናገድ ተገደዋል። ቡራዩም ጣፋጭ ሦስት ነጥቡን በተከታታይ ማሳካት ችሏል።
ምንጭ:ሶከር ኢትዮጵያ